The Neighbor-Love Movement
ስለ መጽሐፉ
ባልንጀራዬ የተሰኘው መጽሐፍ እግዚአብሔር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እኛን መውደዱንና፣ የወደደን አምላክም በወደደን ፍቅር ሌሎችን እንድንወድ መጠበቁን በማሳየት መንገዳችንን እንድናስተካከል ይሞግተናል። ባልንጀራን መውደድ የቅዱሳን መጽሐፍት አንኳር መልእክትና የምንከተለው እግዚአብሔር የሁል ጊዜው የልብ አሳብ መሆኑንን በትንታኔው ያስረዳናል። ይኽ የእግዚአብሔር የሁሌው ሀሳብ ከሰው ፍጥረት ጀምሮ የተገጠ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ የገባው፣ እስራኤል እንዲኖረው የተሰጠው ሕግ፣ የክርስቶስ ትእዛዝ መሆኑንም አሳስበናል። ባልንጀራን መውደድ እንደ ክርስቶስ ተከታይ የተጠራንበት የሕይወት መንገዳችን አካል ነው፣ ይህንን ትእዛዝ አናንቀንም የእርሱ አውነተኛ ደቀ መዝሙሮች ልንሆን አንችልም መልእክቱ ነው።
ስለ ጸሐፊው
ደ/ር ተካልኝ ነጋ የባልንጀራዬ እንቅስቃሴ ኮ-ዳይሬክተር ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እና በኢትዮጵያ የድኅረ ምረቃ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት (ኤገስት) በተጋባዥነት ያስተምራል። ተካልኝ ፒ.ኤች. ዲ በካልቸራል ስተዲስ ኔዜርላንድ ከሚገኘው ከቲልበርግ ዩኒቨርስቲ፣ የማስተርስ ዲግሪዎችን በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ፣ በሳይኮሎጂ፣ በቲዎሎጂ እና በክርስቲያን ሙስሊም ግንኙነት አግኝቷል፡፡ ዶ/ር ተካልኝ “የጸሎት-የንግድ ቤት?!” መጽሐፍ ደራሲ ከመሆኑ ባሻገር፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚዲያ እንግዳ፣ የጥናታዊ ጽሑፎች አዘጋጅ፣ ለመሪዎች ሥልጠና ሰጪ ነው። ዶ/ር ተካልኝ ነጋ ከባለቤቱ ከትኅትና መስፍን እና ከልጃቸው ከሄሴድ ጋር በአዲስ አበባ ይኖራል።
እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራ መውደድ ተያይዘው ይቆማሉ፣ ተያይዘውም ይወድቃሉ።
እግዚአብሔርን መውደድ ባልንጀራን ለመውደድ መሠረት ነው፤ እግዚአብሔርን መውደዳችንም የሚፈተነው ባልንጀራችንን በመውደዳችን ነው። ባልንጀራን መውደድ ጥሎ እግዚአብሔርን መውደድ የሚባል ነገር የለም! እግዚአብሔርን ሳይወዱም እግዚአብሔር ሰውን በሚወድበት ቅድመ ሁኔታ በሌለው ፍቅር ባልንጀራን መውደድ አይቻልም። ባልንጀራችንን ስንወድ እንኳን ክፉ ልናደርግበት ክፉውን መስማት አንፈልግም። ፍቅር ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ያለንን ትስስር ሲገዛ፣ ራሳችንን ለማስቀደም የሚጥረውን ተፈጥሮዋዊ ስሌታችንን ልጓም እናበጅለታለን፤ ሌላውን በማሰብ መኖርም ትግልነቱ ያበቃና በትጋት ልንፈጽመው የምንጠባበቀው ናፍቆታችን ይሆናል።