samedi, 31 octobre 2020 10:40

ባልንጀራዬ፡- አንድነት እና ብዝሃነት ባልንጀሮች ናቸው፤ እኛም እንዲሁ

ከትላንታችን እጅግ የተሻለውን ወስደን አዲስ ነገን ለመገንባት፣ ሌላውን በመግዛት (ሐሰተኛ አንድነት) ወይም በፍቺ (ሐሰተኛ ብዝሃነት) ሌላው እንዲጠፋ የሚፈልገውን  የጦርነት ጉሰማ ማቆም አለብን፡፡

በርካቶች ዛሬ ላይ አንድነት እና ብዝሃነት ጠላቶች ናቸው የሚል ቅድመ እሳቤ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ በፖለቲካው እና በሃይማኖቱ መስክ ሰዎች “የአንድነት ቡድን” እና “የብዝሃነት ቡድን” በሚል ምድብ ሲፈራረጁ ደጋግመን የምንሰማው፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የሁለትዮሽ ጎራዊ አገላለጽ፣ አንድነት እና ብዝሃነት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ለመሰልጠን  ጦርነት የከፈቱ ጠላቶች አድርጎ ያቀርባቸዋል፡፡

እውነታው ግን ከዚህ ይልቅ ቀልብን የሚስብ እና የሚሞግተን ነው፤ ይኸውም አንድነት እና ብዝሃት ባልንጀሮች መሆናቸው ነው፡፡ አንዳቸው ሌላኛቸውን ደግፈው ያኖራሉ፤ አንዳቸው ያለሌላኛቸውም በጤና መኖር ይቸግራቸዋል፡፡ እስኪ እንደገና ዘልቀን እንመልከታቸው፡፡

አንድነት ብዝሃነትን ይሻል፡፡ ያለ ብዝሃት አንድነት አንድ ዐይነትነት በመሆኑ ራሱን ያጠፋል፡፡ የዚህ ምክንያትም ተመሳሳይነት ባለበት የምናብርለት ነገር ስለሌለ ነው፡፡ የሚቀረው ብቸኛው ነገር ቢኖር የሚጨፈልቅ አሃዳዊነት ይሆናል፡፡ አንድነትን የሚያሰነብተው፣ ምስጢራዊ ቅመሙ ብዝሃነት ነው፡፡

ብዝሃነትም እንዲሁ አንድነትን ይሻል፡፡ ያለ አንድነት፣ ብዝሃነት መነጣጠል በመሆኑ ራሱን ያጠፋል፡፡ በመነጣጠል ውስጥ ሁሉ-ነገረ ይለያያልና፡፡ የሚቀረው ብቸኛው ነገር ቢኖር ፍርክስክሱ ወጥቶ የተበተነ ብዝሃነት ይሆናል፡፡ ብዝሃነትን የሚያሰነብተው፣ ምስጢራዊ ቅመሙ አንድነት ነው፡፡

እንግዲህ፣ ከአብዛኛው ሰው ግምት በተቃራኒ አንድነት እና ብዝሃነት ባላንጣ ሳይሆኑ አንዳቸው ሌላኛቸውን ምሉዕ የሚያደርጉ ባልንጀሮች ናቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ከመፎካከር ይልቅ አንዳቸው ሌላኛቸውን ይደግፉታል፡፡ እኔ እንደውም አንዳቸው ለሌላኛቸው ህልውና የግድ ያስፈልጋሉ እላለሁ፡፡ ያለ አንድነት ብዝሃነት የለም፤ ያለ ብዝሃነትም አንድነት የለም፡፡

የዚህ አስተሳሰብ፣ እንድምታው እጅግ ጥልቅ እና ተራማጅ ነው፡፡ አንዳችን ሌላኛችን ሳንሆን (“ለእነርሱ”) ለአንድነት (“ለእኛ”) መሆን አንችልም፡፡ የምንፈልገው እውነተኛ አንድነት ከሆነ፣ የጎለመሰ ጠንካራ ብዝሃነትን መፈለግ ይኖርብናል፡፡ እውነተኛ ብዝሃነት ከፈለግን፣ እንዲሁም የጎለመሰ ጠንካራ አንድነትን መፈለግ አለብን፡፡ ልክ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንዳለው “ሕይወት እጅግ ውብ የምትሆነው፣ ፈጠራ በተሞላበት መልኩ በሰመረ ኅብር ተቀርኖዎችን ማስተጻማር ሲቻል ነው፡፡”

አንዳንዶቻችን ይህን እውነት አለመቀበላች፣ አንድነት እና ብዝሃነትንም በጦር ዐውድማ ላይ ያሉ ባለጋሮች እንደሆኑ አድርገን መሳላችን፣ ሁለት እኩል ሊካዱ የማይቻሉ እና አደገኛ የሆኑ አስተሳሰቦችን በልቡናችን እንዳዘልን ያጋልጥብናል፡፡ “አንድነት” እንፈልጋለን ስንል በእርግጥ እየፈለግን ያለው አንድ ዐይትነትን ነው፤ ፍላጎታችን ሌሎች በእኛ ውስጥ ተውጠው እንዲጠፉ ነው፡፡ “ብዝሃነት” እንፈልጋል ስንልም እየፈለግን ያለነው መለየትን ነው – ሌሎች ከእኛ ገሸሽ እንዲሉ እና እንዲርቁ፡፡

እንደተመለከታችሁት አንድ ዐይነትነት (የሐሰት አንድነት) እና መለየት (የሐሰት ብዝሃነት) ፍሬ ነገራቸው በእርግጥም ተመሳሳይ ነው፤ ሌሎች እንዲጠፉ ይፈልጋሉ፡፡ ልዩነታቸው እንዲጠፉ የታሰበበት መንገድ ብቻ ነው፡፡ ልዩነቱ፣ በመዋጥ ወይም በማሳደድ አሊያም በመግዛት ወይም በመፋታት መካከል ነው፡፡  “መኖር ያለብን እኛ ነን፤ ስለዚህ የማይመስለን ነገር መወገድ አለበት” የሚል ፍሬ ሐሳብ አላቸው፡፡ ታዋቂው ፈላስፋ ኢማኑኤል ሌቪናስ ከናዚ ማጎሪያ ከተረፉት መካከል ሲሆን፣ ይህንን ዐይነት አስተሳሰብ “የጦርነት አመክንዮ” ብሎታል፡፡

ከዚህ አንጻር ባልንጀራን የመውደድ ጥያቄ፣ በማኅበረሰብ መካከል ስለ “አንድነት” እና “ብዝሃት” የሚደረጉ ውይይቶች መዓከላዊ ጭብጥ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ጥያቄው ግልጽ ነው፡፡ ሁላችንም፣ አንዳችን ለሌላችን የምናስፈልግ፣ እኩል ውድ ዋጋ ያለን ባልንጀሮች ነን? ወይስ አንዳችን ሌላኛችንን ማጥፋት ያለብን ጠላቶች? የተፈጠርነው ለትስስር፣ ለማኅበረሰብ ግንባታ እና ለጋራ ዕሴት ወይስ ለአንድ ዐይነትነት፣ ለመራራቅ እና ለጦርነት?

ከዶ/ር ተካልን ነጋ ጋር በጋራ የምመራው ‘ባልንጀራን የመውደድ እንቅስቃሴ’ እኛ ጠላቶች ሳንሆን ባልንጀሮች ነን የሚል ነው፡፡ አንዳችን ከሌላኛችን ጋር ሕይወት እንዲኖረን እና ለጋራ እሴት ተፈጥረናል የሚል መልእክት አለን፡፡ አንድነታችን በብዝሃነታችን፣ ብዝሃነታችን በአንድነታችን እንጂ በሌላው ላይ በመሰልጠን ወይም በፍቺ አይደለም፡፡

Balinjeraye team, partners, and volunteers at the University of Gondar.
የባልንጀራዬ ቡድን፣ አጋሮች፣ እና በጎ ፍቃደኞች በጎንደር ዩኒቨርስቲ

 

ለዚህም ነው አልማዝን በመለያ ምልክታችን ላይ ያደረግነው፡፡ ሰዎች አልማዝ ናቸው፡፡ ሌላውን የሚያገሉ ኃይላት እንድናምን ከሚፈልጉት በተቃረኒ ባልንጀሮቻችን ከእኛ አያንሱም ከእኛም የተለዩ አይደሉም ብለን እናምናለን፡፡ ሰዎች ውድ ባልንጀሮቻችን ናቸው፤ ከእነርሱ ጋር ጥልቅ ትስስር አለን፤ ከእኛ ጋርም አቻ ናቸው፡፡ ወጣቶች በዚህ መልኩ ሌሎች ሰዎችን እንዲያዩ ማነሳሳትም ብቸኛ አላማችን ነው፡፡

ለዚህም ነው መለያችን በሆነው በአልማዙ ዙሪያ ላይ የአቅጣጫ መለያ መሳሪያ (ኮምፓስ) ምልክት ያለው፡፡ ሰዎችን እንደ አልማዝ መመልከት ስንጀምር ለሕይወታችን የአኗኗር አቅጣጫ አግኝተንለታል፡፡ የት መሄድ እና ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃን፤ የሕይወታችን ካርታ እና ተልዕኮ አለን፡፡

ትልቁ ተግዳሮት ግን፣ የባልንጀራን መውደድ ተገዳዳሪ አስተሳሰቦች፣ የእኛን አቅም ብዙም የማይፈትኑ መሆናቸው ነው፡፡

ሁሉም እኛን ይምሰል ወይም የማይመስለን ይወገድ የሚለው ሐሰተኛ አንድነት እጅግ ቀላል ነው፤ አይከብድም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም እኛን የማይመስለው ይጥፋ የሚለውም ሐሰተኛ ብዝሃነት እጅግ ቀላል ነው፤ አይከብድም፡፡ በዓለማችን ዙሪያ ያሉት ማኅበረሰቦች የሚያሳዩን ይህንኑ ነው፤ ራስን ጣኦት በሚያደርግ አመለካከልት ዙሪያ ሰዎችን ማሰባሰብ እና ማንቀሳቀስ በእርግጥም ቀላል ነው፡፡ መንገዱ ተበደልኩ ማለት፣ ሌሎችን መክሰስ እና ድንገተኛ የነውጥ ማዕበል አስነስቶ ሌሎችን ማጥቃት ነው፡፡

ጨለማው እና እንስሳዊው የሰው ማንነት ጦርነት ለማወጅ ተዘጋጅ በሚለው ጉትጎታ ይሳባል፡፡ ይህ ማንነት ደስታው ብልሹ ስለሆነ በሌላው ላይ መሰልጠን (ትዕቢት)፣ ሌላውን መግዛት (ኃይል) እና  ሀብትን በብቸኝነት መቆጣጠር (ትርፍ) ይፈልጋል፡፡ ሲግመንድ ፍሮይድ Civilization and Its Discontents (1930) በተሰኘው መጽሐፉ በሚገርም መልኩ “ሰዎች ራሳቸውን በተሳሳተ መለኪያ ሲለኩ፣ ሁሉም በሕይወት ትልቅ ትርጉምና እጅግ ዋጋ ያላቸው ነገሮች እየናቁ፣ ኃይልን፣ ስኬትን እና ባለጸግነትን ፍለጋቸው ያደርጋሉ፤ እነዚህንም በሕይወት ዘመናቸው ያሳኩትን ያደንቃሉ፤” ሲል ጠማማውን የሰውን ደስታ ገልጾታል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ፣ ውብ ከሆነው ቀሊልነቱ እና ከሚያጎናጽፈው ደስታ በመለስ ያለው ባልንጀራን የመውደድ አስተሳሰብ እጅግ ውስብስብ እና ሞጋች ነው፡፡

ባልንጀራን መውደድ ውስብስብ እና ሞጋች የሆነበት ምክንያቱ በመሠረታዊ እሴቶቻችን፣ ተግባሮቻችን እና ተቋሞቻችን ላይ የሞራል ለውጥ እንድናመጣ ግድ ስለሚለን ነው፡፡ ይህ ልውጠት መለያው ብዝሃነት ሲሆን በሌላው ሰው ፈንታ ራስን ማስቀመጥን (ሌሎችን መንከባከብ)፣ ወይይት ማድረግን (ከሌሎች ጋር መነጋገር)፣ መተማመንን (ሌሎችን ማመን)፣ መተባበርን (ከሌሎች ጋር መሥራት)፣ ተጠያቂነትን (አንዳችን ለሌላኛችን ተጠያቂነትን ማስፈን)፣ እና ፈጠራን (ለድሮ ችግሮች አዲስ መንገድ መፈለግን) በአንድ ላይ በጥምረት የያዘ ነው፡፡

እነዚህ በጎ ባሕሪያት ባልንጀራን የመውደድ ውጤቶች እንጂ፣ ዝም ብሎ የማይጨበጥ ስሜትና ደስተኛ እንዲያረጉን በሚል የምናስባቸው ሐሳቦች አይደሉም፡፡ ባልንጀራ መውደድ ለሌሎች ሰዎች ደኅንነት ከልባችን ተግባራዊ ሥራ ላይ ለመሳተፍ መፍቀድን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያህል በ2014 ታይምስ ኦፍ ለንደን ባልንጀራዬን መውደድ ለእንግሊዝ አገር ኢኮኖሚ 3 ቢሊዮን ፓውንድ እንደጨመረላት አስነብቦናል፡፡ በ2018 የተደረገ ሌላ ጥናት እንዲሁ ለአሜሪካን ኢኮኖሚ ባልንጀራን መውደድ 8.8 ቢሊዮን ዶላር እንዳስገኘላት አመላክቷል፡፡

Balinjeraye exists to cultivate this transformative unity and diversity rooted in neighbor-love among Ethiopian young people.የባልንጀራዬ ውጤቶች: ክብር+ ውይይት + መተማምን + መረዳዳት + ፈጠራ = ማበብ (መፍካት)

የባልንጀራዬ አላማ ባልንጀራን በመውደድ ላይ የተመሰረተውን ለዋጭ አንድነት እና ብዝሃነት በወጣት ኢትዮጵያውያን መካከል መኮትኮት ነው፡፡

ባልንጀራዬ ሌሎች ሰዎች ዋጋ እንዳላቸው ባልንጀሮች እንጂ፣ እንደ ባይተዋሮች እና እንደ ጠላቶች መታየት የለባቸውም በሚል የሚፈረም የቃል ኪዳን ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ቃል ኪዳኑ ባልንጀራን መውደድ ምን ዐይነት መሰጠትን ከአኗኗራችን እንደሚጠይቅ ያሳያል፡፡ ከ3000 የሚበልጡ ወጣት ኢትዮጲያውያን ከህዳር 2012 ዓ.ም. ጀምረው ይህንኑ  የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡ ከተለያየ ብሔር፣ ሃይማኖትና የእድሜ ክልል የተወጣጡ ኢትዮጲያውያን ቃል ኪዳናችን አንብበው በፈገግታ “አዎን! ዛሬ የሚያስፈልገን ይሄ ነው” ሲሉ ስንሰማ ሁሌም እንበረታታለን፡፡ ቃል ኪዳናችንን የፈረሙትን ሰዎች ዝርዝር ስትመለከቱ ልትደነቁ ትችላላችሁ፡፡

በዕለት ተዕለት ኑሯችንም የሰውነት አካላችን በማሰልጠን የምንተገብራቸውን ሰባት ተግባራትን አስተዋውቀናል፡-

  1. በዐይኖቻችን ሌሎች ሰዎችን እንደ ውድ ባልንጀሮቻችንን መመልከት፤
  2. በጆሮዎቻችን በትዕግስት ሌሎችን ማድመጥ፤
  3. በአንደበቶቻችን በአክብሮት እና በእውነት ከሌሎች ጋር መነጋገር
  4. በእጆቻችን ሌሎችን ከመጉዳት ይልቅ መርዳት፤
  5. ለሌሎች ደስታ እና ህመም ልቦቻችንን መክፈት፤
  6. በእግሮቻችን ካለንበት ንፍቀ ክበቦቻችን እየወጣን ከሌሎች ጋር ትስስር መፍጠር፤
  7. አዕምሮዋችንን በመጠቀም አብረን ፈክተን እንድናብብ እሴቶቻችን ከተግባሮቻችን ጋር ማጣጣም፡፡

እነዚህ ተግባራት ገንዘብ፣ ቴክኖሎጂ ወይም የኢንተርኔት መረብ አይፈልጉም፡፡ ከእኛ የሚፈልጉት፣ በፍቅር ኃይል አቅም ያገኙ የሰውነት አካሎቻችንን ብቻ ነው፡፡




እነዚህ የባልንጀራዬ ቃል ኪዳን እና ተግባሮቻችን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግረኛ ተዘጋጅተዋል፡፡ እነርሱን ለማግኘት (www.balinjeraye.org/sign) ይመልከቱ፡፡

 

ለባልንጀራዬ ቃል ኪዳን እና ተግባራት ራሳቸውን የሰጡ ሰዎች ባልንጀራን የመውደድ አምባሳደሮች ናቸው፡፡ እነርሱ በእለት ተእለት ኑሯቸው እጅግ ጥንታዊ የሆነውን እና ከዚህ ዘመን ባሻገር ያለውን ነገር አጥርቶ ማየት የሚችለውን የሰውነት ተምሳሌትነትን የሚከተሉ ሰዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጲያ የእህል ንግድ ሥራዎች ኮርፓሬሽን መስራች የሆኑት ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን የእንቅስቃሴያችን መከፍቻ አምባሳደር በመሆናቸው ክብር ተሰምቶናል፡፡ ሌሎች በርካታ ተጽእኖ እየፈጠሩ ያሉና ወደ መሪነቱ በቅርቡ እየመጡ ያሉ መሪዎች በግል እና በሙያዊ ሕይወታቸው ባልንጀራን መውደድን ለመተግበር ቃል ገብተዋል፡፡

የባልንጀራን መውደድ እንቅስቃሴ ምሰሶ ከሆኑት ከቃል ኪዳኖቻችን፣ ከተግባሮቻችን እና ከአምባሳደሮቻችን ባሻገር በርካታ “ቀጣይ እርምጃዎችን” አሰናድተናል፡፡ እነዚህም እንደ ባልንጀራ የምናያቸውን ሰዎች አድማስ ለማስፋት በሚል ያዘጋጀናቸው የ30 ቀን  የጥሞናዊ አሰላስሎዎች፣ የመጀመሪያውን የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ ባልንጀራን የመውደድ የሥነ ምግባር ክርስቲያናዊ ትምህርቶች (ኢስላማዊው የሥነ ምግባር ኮርስ በዝግጅት ላይ ነው)፣ በዶ/ር ተካልኝ የተዘጋጀው ባልንጀራየ የተሰኘ ፈር ቀዳጅ መጽሐፍ፣ እና መደበኛ ያልሆነ ነገር ግን ፍቅር፣ ፍትሕ እና ብልጽግናን በሥራ መስካቸው መአከላዊ ማድረግ የሚፈልጉ የግለ ሰቦች እና የተቋማት ኢመደበኛ አጋርነት መድረኮችን ያካትታሉ፡፡

የባልንጀራን መውደድ የውይይት ዝግጅቶችን በክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እየተማሩ ላሉ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በማዘጋጀት፣ ወጣት መሪዎች የባልንጀራን መውደድ አምባሳደሮች እንዲሆኑ ጋብዘናቸዋል፡፡ ዘ ጋርዲያን 35000 ያክል ተማሪዎች በቅርብ ወራት ከግጭቶች የተነሳ ዩኒቨርስቲዎችን  ጥለው በሄዱበት ሁኔታ ሰላምን ለማምጣት ለምንጫወተው ሚና እውቅና ሰጥቶታል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ከ800 በላይ ተማሪዎች በጋለ ስሜት ቃል ኪዳናቸው ከፍ አድርገው መያዛቸውን በመመለክት የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማትን ሚኒስተር ወክለው የተሳተፉት ሰው “ ይህንን እንቅስቃሴ በኢትዮጲያ ውስጥ ወደሚገኙ 45 ዩኒቨርስቲዎች ትወስደዋለህ ስል ተስፋ አደርጋለሁ! እንዲህ ዐይነት ነገር ከዚህ በፊት ዐይቼ አላውቅም!” ብለውኛል፡፡

 

የጂጂጋ ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነት ኦፊሰር ጀማል ሀሺ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ከዶ/ር አብዲ አህመድ በኋላ የቃል ኪዳን ሰነዳችንን ለፈረሙ ለ500 ተማሪዎች “ዛሬ የፍቅር ክትባት ወስደናል!” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

በአዲሳ አበባባ ውስጥ አያሌ ትናንሽ ዝግጅቶችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር አካሂደናል፡፡ አሁን ደግሞ “ባልንጀራን መውደድ 101” የተሰኘ ዝግጅትን በአዲስ አበባ ለማድረግ ራሳችንን እያሰናዳን ነው፡፡ ዝግጅቱ ሁሉን ያሳተፈ ይፋዊ ሕዝባዊ ውይይት ማድረግ ላይ በማተኮር፣ መሪዎች  በተሰማሩባቸው የተለያዩ የሥራ መስኮች ባልንጀራን መውደድን እንዲተገብሩ ማነሳሳትን ያለመ ነው፡፡ 

ወጣቶችን የሚያነሳሳ የማኅበራዊ ገጽ የሚዲያ ዕለታዊ ዝግጅቶቻችንን ሚሊዮኖችን ስበዋል፡፡ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ካሉ እንደ ኢትዮጲያን ሄራልድአዲስ ማለዳፎርቱንአዲስ ስታዳርድቪ ኦ ዔዘ ጋርዲያን እና ዘ ኢኮኖሚስት ጋር ትስስር ፈጥረናል፡፡

ህልማችን የባልንጀራን መውደድ ቆንስላ (መዓከል) በአዲስ አበባ በመክፈት ጥልቅ አሳቢነትን፣ ፈጠራ የተሞላ ዐይነ ህሊናን፣ ለፍቅር፣ ለፍትህ እና ለብልጽግና በተግባር መሰጠትን ቀጣይነት ባለው መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ መኮትኮት ነው፡፡ መዓከላችንም በየቀኑ እንኳ ባይሆን ሳምንታዊ የሕዝባዊ ውይይቶች፣ የሌክቸሮች፣ የአጫጭር ትምህርቶችን፣ የሜንተሪንግ እና የፌሎሺፕ ዕድሎችን ይሰጣል፡፡ ብቅ ብቅ የሚሉ ወጣት መሪዎችን የሚያነሳሳ እና የሚያጠናክር የአገልግሎት ፕሮጀክቶችም ይኖሩናል፡፡ እጅግ የሚገርመው የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ እንዲህ ዐይነት መዓከል አለመኖሩ ነው፡፡ ለዚህ ሥራ ፈር ቀዳጆች መሆን እንፈልጋለን፡፡

የቀድሞው የቼኮዝላቫኪያ ፕሬዝዳንተ ቫክላቭ ሀቫል፣ “ማንነት እስር ቤት ሳይሆን ከሌሎች ጋር እንድንወያይ የሚጋብዝ ጥሪ ነው፡፡ ሌላውን ሰው መውደድ፣ እኔ እበልጥ እያሉ እርስ በእርሳቸው በሚፎካከሩ ባህሎቻችን ሁሉ ዘንድ ያለ መአከላዊ ትእዛዝ ነው” በማለት በሚያስገርም ሁኔታ ገልጾታል፡፡

ሀቫል ልክ ነበር፡፡

ሙሴ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ. . . እንግዳም እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥” (ዘሌዋውያን 19፥18፣ 34)፡፡

ኢየሱስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉዋችሁ መልካምን አድርጉ” (ሉቃስ 6፥27) ሲል አስተምሯል፡፡

ሙሀመድ “በቅርብ እና በሩቅ ላሉ ባልንጀሮቻችሁ መልካምን አድርጉ” (ቁራን 4፡36) እና “የበደሉዋችሁን ይቅር በሉ” (ሀዲስ አል ጠባሪ 282) ሲል አስተምሯል፡፡

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር “ፍቅር ግላዊ እና ማኅበራዊ ለውጥን ለማምጣት እጅግ የተዋጣለት መሣሪያ ነው፡፡.... ከመቼውም በበለጠ ደግሞ የሰው ዘር ሁሉ እና አገራት ባልንጀራ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዓለማቀፋዊ የባልንጀራነት ፓሊስ የዓለማችንን አይቀሬ የለቅሶ እንጉርጉሮን ወደ ፈጠራ የተሞላበት የፍጻሜ መዝሙር አድርጎ ለመቀየር የተደረገ የሕይወት መንገድ  ነው” ሲል ገልጾታል (ስትሬንግዝ ቱ ላቭ)፡፡

አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች ዲሞክራሲን ይደግፋሉ፡፡ ባልንጀራን በመውደድ ውስጥ፣ የሚያስገርም አንድነትን በብዝሃት፣ ብዝሃነትንም በአንድነት ውስጥ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ትውፊቶች ደግሞ 110 ሚሊዮን አከባቢ የሚገመቱትን፣ 98 በመቶ የሚሆኑትን ኢትዮጲያውያንን ይወክላሉ፡፡ 

98 በመቶ የሆነችውን ኢትዮጲያን በዐይነ ህሊናችሁ ተመልከቱ! ከዚህ በበለጠ አንድነት በብዝሃነት የሚበልጽግበትን ዕድል ማሰብ ያዳግታል፡፡ ሀቫል እንዳለው ባልንጀራን መውደድ “እኔ እበልጥ እያሉ በሚፎካከሩ ባህሎቻችን ውስጥ ያለ መአከላዊ ትእዛዝ ነው፡፡” ብዝሃነት እንዳላቸው እና አንድ እንደሆኑ ባልንጀሮች እኛ የሰው ልጆች ባልንጀራን መውደድ ለመልካም ሕይወት  የምንጋራው የሞራል ራዕይ ነው፤ እያንዳንዳችን የተሰጠን ኃላፊነት ከፍ ያለ የሕይወት ትርጉምን፣ ዓላማን እና ብልጽግናን የምናገኝበት ተስፋችን ነው፡፡

ግለሰቦችን እና ማኅበረሶችን፣ በአዲስ መልኩ የሚያነሳሳውን እና የሚሞግተውን ባልንጀራን የመውደድ እንቅስቃሴን በሁሉ ዘንድ የምናነብርበት ጊዜ ላይ እንዳለን እናምናለን፡፡ እያንዳንዳችን ከልባችን ፈቅደን በተግባር ለጋራ ደኅንነታችን መሥራት አለብን፡፡ ወደ ጦርነት ከሚወስደን ተስፋ የለሽና ትርፉ ዜሮ-ድምር ከሆነው ቁማር ይልቅ፣ እውነተኛ አንድነትንና ብዝሃነትን ለማስፈን ልከኛው መንገድ ይሄ ነው፡፡

ከትላንትናችን መልካሙን ወስደን ለምንገነባው አዲሱ ነገ ጦርነት ከፍቶ ሌላውን በመግዛት (ሐሰተኛ አንድነት) ወይም በፍቺ (ሐሰተኛ ብዝሃነት) ሌሎችን ማስወገድ መፈለጋችንን ማቆም አለብን፡፡ እውነታው እኛ ባልንጀሮች ነን እንጂ ጠላቶች አይደለንም፡፡ ለእርስ በእርሳችን ካልሆንን፣ እኛነታችንን እናጠፋለን፡፡ አንዳችን ሌላኛችን እንድናብብ የምናስችል ሚስጥራዊ ቅመሞች ነን፡፡

ታዋቂው የሀርቫርድ ዮኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሄነሪ ኖዊን ቁስለኛው ፈዋሽ  በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፣ እንዳሳየን “የእያንዳንዱ ሰው ፊት የባልንጀራው ፊት ነው፡፡” ሁላችንም በእያንዳንዳችን ዓለም የአንድነታችን እና የብዝሃነታችን መገለጫዎች ነን፡፡ ሁሉም ባልንጀሮች ናቸው (አንድነት)፤ አንዱ ከሌላው ልዩ ነው፤ መቼም አንድ ዐይነት አይሆንም (ብዝሃነት)፡፡

የኢትዮጲያን እና በውስጧ የሚኖሩ የ110 ሚሊዮን ባልንጀሮችን የወደፊት እጣ ፈንታ ስናስብ ደስ ይለናል፡፡

ልክ እንደ ማህቡብ ኡል ሀቅ “የአገር እውነተኛ ሀብት ህዝቦቿ” እንደሆኑ እናምናለን፡፡ 70 ሚሊዮን ወጣቶች ያሏት ኢትዮጵያ እንደምን ባለጠጋ ናት! ወጣቶቿ ቢኮተኮቱ እና ቢነሳሱ፣ በሥራዎቻቸው የእያንዳንዳችንን አልማዝነት አስበው ቢንቀሳቀሱ የኢትዮጲያ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊመስል እንደሚችል በዐይነ ህሊናችን እንሳለው እስኪ!

ከኡል ሀቅ  ጋር አብረን፣ “ይህ ቀላሉና ኃያሉ እውነት፣ ብዙ ጊዜ ቁስ እና ገንዘብን በማሳደድ ሂደት ውስጥ ይረሳል” እንላለን፡፡ የተሻለ እና የሚሻል እውነት በፊታችን ቆሟል፡፡ ብዝሃነትን እና አንድነትን በመውደዱ እያንዳንዱ ባልንጀራ የሚሻል ምልዑ ሕይወት ይኖረዋል፡፡

ዛሬ የትም ሁኑ፣ የትም ኑሩ፣ በአክብሮት ቃል ኪዳናችንን እንድትፈርሙ፣ ተግባሮቻችንም የዘውትር ሥራችሁ እንድታደርጉ እና የባልንጀራን መውደድ አምባሳደሮች እንድትሆኑ እንጋብዛችኋለን፡፡ እንቅስቃሴያችንን ይቀላቀሉ፡፡ በኢትዮጲያ ብሎም በዓለም ላሉ ባልንጀሮች፣ ፍቅር፣ ፍትሕ እና ማበብን የምናሰፍንበት ዓለም ለመፍጠር የእርሶን መነሳሳት ከእኛ ጋር በማጣመር ይሥሩ፡፡

ይህ ጽሑፍ የጸሐፊው ምልከታ ነው፡፡ ግልጽ የእውነታ ስህተቶች ካሉበት ግን የኢትዮጲያ ኢንሳይት ያርማቸዋል፡፡

ዶ/ር አንድሪው ዲኮር የባልንጀራየ፡- ባልንጀራን የመውደድ እንቅስቃሴ መስራች ዳይሬክተር ሲሆን እንቅስቃሴው ወጣት ኢትዮጵያውያን ሌሎችን ያለ አንዳች ገደብ እንደ ባልንጀራቸው እንዲያዩዋቸው የሚያነሳሳ ነው፡፡ በፌስቡክ፣ በቴሌግራም፣ በዬቱዩብ እና በኢንስታግራም ላይ ይከተሉን››  

ስለ ጸሐፊው

ዶ/ር አንድሪው ዲኮርት፣  ፒ.ኤች.ዲውን በሪሊጂየስ ኤንድ ፓለቲካል ኢቲክስ ከቺካጎ ዩኒቨርስቲ ያገኘ ሲሆን በዊተን ኮሌክ፣ በኢትዬጲያ የሥነ መለኮት ድህረ ምረቃ ኮሌጅ እና በቦን ዩኒቨርስቲ አስተምሯል፡፡ Bonhoeffer’s New Beginning: Ethics After Devastation የተሰኘ መጽሐፍም ደራሲ ነው፡፡


Originally published on Ethiopia Insight.